ዕለተ ዓርብ (ስቅለት)
“አንዱ ስለሁሉ ሞተ” (2ቆሮ 5÷14)
ይህንን ቃል የተናገረው ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በፃፈው መልዕክቱ ነው፡፡ኢየሩሳሌም የፋሲካን በዓል ለማክበር በሽርጉድ ላይ ነች፡፡ የፋሲካ በዓል እስራኤላውያን ከ430 ዓመት የግብፅ ባህነት ነፃ የወጡበትን ቀን በማስመልከት የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡ ታዲያ ይህንን የደስታ በዓል ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ የህዝብ ምርጫ የሆነ አንድ እስረኛ መፍታት የሮማ ገዢዎች ልማድ ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም የሚገኘውና በሮማ መንግስት ሥር የሆነው እስር ቤት ብዙ እስረኞችን ይዞ ነበር፡፡ በርባን ሞት የተፈረደበትና የሞቱን ዕለት የሚጠባበቅ እስረኛ ሲሆን አደገኛ ወንበዴ በመሆኑ በብርቱ ይጠበቅ ነበር፡፡
መስፍኑ ጲላጦስ ንፁሑን ሰው አሳልፎ ለመስጠት ህሊናው ዳግመኛም የሚስቱ ማስጠንቀቂያ ይታገለው ነበር፡፡ በዚያ በአል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ዘንድ ለገዢው ልማድ ነበረው፡፡ ጲላጦስም በጣም የሚያስጨንቃቸው የነበረውን በርባንንና ኢየሱስ ክርስቶስን አነጻጽሮ ማንን ልፍታላችሁ? አላቸው፡፡ መቼም በርባንን አይመርጡም ብሎ ነው፡፡ በርባን በወንበዴነቱና በሽፍታነቱ የታወቀ ህዝቡንም ሲያስጨንቅ የኖረ፣ ቋንጃ የቆረጠ፣ ሁሉም እስራኤላዊ የተማረረበት ሰው ነው፡፡
እነርሱ ግን በቅንዓት ታውረዋልና የሚያድናቸውን ሳይሆን የሚያስጨንቃቸውን በርባንን መረጡ፣ የፈወሳቸውን ሳይሆን የቀማቸውን፣ ሰላም የሰጣቸውን ሳይሆን ያወካቸውን፣ አምላካቸውን ሳይሆን ዘራፊያቸውን መረጡ፡፡ የዓለም ምርጫ ከዚህ አያልፍምና፡፡
በርባን ከእስር ቤት ይፈታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ቦታ ይግባ/ይሰቀል/አሉ፡፡
(ማቴ 27÷17)
ወታደሮችም በርባንን ሊፈቱ ወደእስር ቤት ሲገቡ በርባን ሳይደነግጥ አልቀረም፡፡ በርባን ሆይ በነፃ ተለቀሐል አሉት፣ እርሱም እኔ በነጻ እንድወጣ ምክንያት የሆነኝ ምንድነው ቢላቸው እነርሱም እንደዋዛ ኢየሱስ በአንተ ፈንታ ሊሞት፣ አንተ ግን ነጻ ልትወጣ ተወስኗል አሉት፡፡ በርባንም በጣም ተደስቶ እስረኞችን ሲሰናበት “በሉ ሰላም ሁኑ ኢየሱስ በእኔ ምትክ ሊሞት እኔ ደግሞ በሕይወት እንድኖር ተፈርዷል”
እያላቸው ከወህይኒ ወጣ፡፡
“አንዱ ስለሁሉ ሞተ”
ሞት ምንድነው?
አራት አይነት ሞት አለ፡-
1. ሞተ ሥጋ /የሥጋ ሞት/ ዕርደተ መቃብር ነው፡፡ ሥጋም ወደ መሬት ነፍስም ወደ እግዚአብሔር ትሄዳለች፡፡ (መክብብ 12÷7)
2. ሞተ ነፍስ /የነፍስ ሞት/ እሱን የማትሰማ ነፍስ ትሞታለች፡፡ (ዘዳ.18÷15 የሐዋ.3÷23)፣(ማቴ.25÷41)
3. ሞተ ሐጢአት /የሐጢአት ሞት/የሐጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፣
(ሮሜ 6÷23)፣(ቆላ.1÷22)፣ (ኤፌ.2÷1)
4. ሞተ ሕሊና /የሕሊና ሞት/
አምላካችን መድኃኒታችን ለምን ሞተ?
1. ቅጣታችንን ተቀብሎ ሞተ፡- የሁላችንንም በደል በራሱ ላይ አኖረ፡፡ (ኢሳ.53÷6)ስለጽድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና (ሮሜ 5÷6) ተብሎ እንተጻፈው፣ የእኛን የበደል ቅጣት እርሱ ወስዶ ተቀጣ፡፡ ማን ነው የሌላውን የቅጣት ወንጀል በዚህ ዘመን የሚወስድ? የሌላውን ቅጣት እንኳን ባንወስድ እርስ በእርሳችን መወነጃጀላችንን፣ መነካከሳችንን መቼ ተውን? እርሱ ተቀጥቶ በመስቀል ላይ እኛን ነጻ አወጣን፡፡ ቅጣታችንን ሙሉ በሙሉ ወሰደ፡፡
2. የእኛን ሞት ሞተ፡- በአንድ ሰው ምክንያት ሞት ወደዓለም ገባ ተብሎ እንደተጻፈው (ሮሜ 5÷15) የሰው ልጅ የአምላኩን የእግዚያብሔርን ትዕዛዝ ለማፍረሱ ምክንያት 5,500 ዓመት ሞት ተፈረደብን፡፡ ሞት ገዛቸው ተብሎ እንተጻፈው፡፡ ሰለ እኛ የእኛን ሞት ተገብቶ ሞተ፡፡ ሐጢአት ያላወቀውን እርሱ ስለ እኛ ሐጢአት አደረገው፡፡ (2ኛቆሮ÷15-21)ብዙ ሰዎች ሞተዋል፣ ተቀብረዋል፣ የእኛን የሐጢአት ሞት ግን መቀየር አልተቻላቸውም፡፡ በመቃብራቸውም ውስጥ የአጥንት ቅሪት አለ፡፡ ጐለጐታ ብንሔድ የጌታ መቃብር በታሪክ እስከዛሬም ድረስ ባዶ ነው፡፡ ከተለያዩ አለማትም የሚመጡ ይህንኑ ባዶ መቃብር አይተው ነው የሚመለሱት፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ለየት የሚያደርገው፡-
- የሰማያትነት ሞት አይደለም፡፡
- በድንገተኛ አደጋም አይደለም የሞተው፣ የእኛን ሞት ነው የሞተው፡፡
3. ፈውስ እናገኝ ዘንድ ሞተ፡- በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡ (ኢሳ.53÷5) እርሱ የሾህ አክሊል ተደፍቶበት እኛን የክብር አክሊል ደፋልን፡፡ ጐኑን በጦር ተወግቶና ቆስሎ ለዘለአለም ፈወሰን፡፡ ተጠማሁ እያለ እኛን የሕይወት መጠጥ አጠጣን፡፡ ማነው ለሌላው እየቆሰለ ሌላውን ሰው የሚያድን፣ የሚፈውስ፣ በዚህ ዘመን ይገኝ ይሆን? መፈወሱና መቁሰሉ ቀርቶ ማቁሰሉንና ማሳዘኑን በተውን መልካም ነበር፡፡
4. ገነትን እንወርስ ዘንድ መርገማችንን ወስዶ ሞተ፡- በእንጨት የተሰቀለ የተረገመ ነው፡፡ ተብሎ እንደተጻፈው (ዘዳ.21÷23)የመጨረሻው የእርግማን ምልክት ነው ተብሎ በሚታሰበው በመስቀል አምላካችን ተሰቀለ፡፡ የስቅላት ቅጣት የተጀመረው በፋርሳውያንና በፌንቃውያን ነው፡፡ በተለይ ግን የተጠቀሙበት ሮማውያን ናቸው፡፡ የሮም ዜጋ የሆነ ግን በምንም ምክንያት በስቅላት አይቀጣም፡፡ ይህ አይነቱ የሞት ቅጣት በጣም አስነዋሪ ወንጀሎችን በተለይም ዓመጽና ሁከት የሚያስፋፉ አይነት ወንጀል ፈጻሚዎች ብቻ በመስቀል የሚቀጡበት ነበር፡፡ አምላካችን በደል አልተገኘበትም፣ ወንጀልም አልሰራም፣ ሁከትንም አልፈጸምም አላነሳሳም፡፡ የዓመጽም ሰው አልነበረም፡፡ ጲላጦስ ሳይቀር መስክሯል፡፡ “ምንም በደል አላገኘሁበትም ነው ያለው”፡፡ በዛም ዘመን መስቀል የመጨረሻው የውርደትና የመከራ ምልክት ነበር፡፡ አሁን ግን መስቀል የድላችን ምልክት፣ ሰላማችንን ያገኘንበት፣ ጥል የተገደለበት ነውና እናከብረዋለን፡፡ (ቆላ.3÷14)፣ (ኤፌ.2÷20)፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሁላችን ሞተ
ሞቱም ቅጽበታዊ ሳይሆን ስቅለቱንና ሞቱን አስቀድሞ አረጋግጦ ተናግሯል፡፡ (ማቴ.16÷21)፣ (ማቴ.20÷17)፣ ለደቀመዛሙርቱ፡-
- የበጉ መታረድ ለመጥምቀ መለኮተ ዮሐንስ (ዮሐ.1÷29)
- ስለ በጐቹ ሕይወትን መስጠቱ (ዮሐ.10÷11-18ዓ)
- ስለ ስቅለቱ ለሕግ አዋቂው ለኒቆዲሞስ (ዮሐ.3-14)
መልዕክት
አንዱ ስለሁላችን ሞተ፣ የእኛን ቅጣት ወሰደ፣ ሞታችንን ሞተ፣ ገነትን እንድንወርስና በሕይወት እንኖር ዘንድ ሞተ፡፡ መርገማችንን ወሰደ፡፡ ወገኖቼ የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅላት ሞት ስናስብ የተጣላን ታርቀን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መሞት የሰው ልጆች የጥል ግድግዳ ፈርሶ ፍቅር የተመሰረተበት ዕለት ነውና፡፡ እኛም ጥላቻንና መነቃቀፍን በማስወገድ መኖር፣ አምላካችን ተፈጸመ ብሎ የተናገረበት ዕለት ነው፡፡ የፍቅርን እናት እናታችን ድንግል ማርያምን በደቀመዝሙሩ በዮሐንስ አማካኝነት በስጦታ የተቀበልንበት እለት ነው፡፡ (ዮሐ.19÷36)፣
- ስቅለቱንና ሞቱን ስናስብ በቀራንዮ የተደረገልንን ውለታና ቸርነት በፍፁም ልንዘነጋው አይገባም፡፡ ሁላችንም ከቤተክርስቲያን ሳንለይ በመጾምና በመጸለይ፣ የተጣላን በመታረቅ፣ ፍቅርን በመመስረትና በመስገድ ልናሳልፍ ይገባናል፡፡
- ስቅለት የ5500 ዓመት የእዳ ደብዳቤያችን የተሠረዘበትና የተወገደበት ፣መርገማችን የሐጢያታችን ቀምበር የተሰበረበት፣ የሞትና የጨለማ መጋረጃ የተቀደደበት፣ ፍፁም ፍቅር የተመሰረተበት ዕለት ነውና በየትኛውም ዓለም የምንኖር ወገኖች ከሁለም በላይ የሚበልጠው ፍቅር ነውና ፍቅርን ገንዘብ እናድርግ፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
- ለብርሃነ ትንሣኤው ያድርሰን፡፡
ለዛሬ የመረጥኩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ
“እርሱም ሐጢአት አላደረገም፣ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፣ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፣ መከራንም ሲቀበል አልዛተም፣ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፣ ለሐጢአት ሞትን፣ ለጽድቅ እንድንኖር እራሱን ራሱ በሥጋው ሐጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፣ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ፣ እንደበጐች ትቅበዘበዙ ነበርና፣ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል፡፡
(1ኛ ጴጥ.2÷22-25)ይቀጥላል፡፡
ቃለ ሂወት ያስማልን
ReplyDeleteእሜንንን