Tuesday, April 17, 2012

መልካም ትንሳኤ


“እንደተናገረ ተነስቷል” (ማቴ.28÷6)

እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ወረደ፣ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፣ እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፡፡ እንደተናገረው ተነስቷልና…በዚህ የለም…ኑና እዩ አላቸው፡፡ ስለ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አራቱ ወንጌላውያን በመጽሐፋቸው ስለ ትንሣኤው ምስክርነት በመስጠት አረጋግጠው ጽፈዋል፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት የመነሳቱ ማረጋገጫው ምንድነው?
- በዕለተ እሁድ ከሞት በተነሳበት ቀን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጥ ታይቷል፡፡ ለማርያም መቅደላዊት (ዮሐ.20÷11)
- ለሌሎች ሴቶች (ማቴ.28÷9) ለሁለቱ የመኤማሁስ መንገደኞች (ሉቃ.24÷13)

የኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሳቱ ለእኛ ለክርስቲያኖች ያለው ጥቅም ምንድነው?

ከሞት የመነሳታችን ማረጋገጫ ነው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሞተና እንደተነሣ ካመንን እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚያብሔር ከራሱ ጋር ያወጣቸዋልና(ያስነሳቸዋል)፡፡ (1ኛተሰ.4÷13)፣

አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነስቷል፡፡ ሞት በሰው በኩል ስለመጣ ትንሣኤውም በሰው በኩል ሆኗል፡፡ (1ኛ ቆሮ. 15÷21)ሞት ድል በመነሳት ተዋጠ ተብሎ እንደተጻፈው (1ኛ ቆሮ 15÷54)፣

- የኢየሱስ ትንሣኤ የስብከታችን ማረጋገጫ ነው፡- ትንሣኤ ሙታን ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፣ ክርስቶስ ካልተነሣ ስብከታችን ከንቱ ነው፡፡ (1ኛ ቆሮ.15÷12)፣

- ትንሣኤው የእምነታችን ማረጋገጫ ነው፡- ክርስቶስ ካልተነሣማ እምነታችን ከንቱ ነው፡፡ (ቆሮ 15÷17) ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል ሲነሣ መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በስልጣኑ ተነሣ፡፡ እንዲህ ተብሎ መቅዱሳት መጻሕፍት እንተጻፈው፣ ወተንሣአ እግዚያብሔር ከመዘንቃህ እንዋም ወከመ ኃያል ወህዳገ ወይን ወቀተለ ጸሮ በድሬሁ፣ እግዚያብሔር ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ተነሣ፡፡ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያል ሰው፣ ጠላቶቹንም በኋላው ገደለ፡፡

- (መዝ.67÷65)በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን ብዙ ሰዎች ከሞት እንደተነሱ ታሪካቸው ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ሁሉም ግን አስነሺ አላቸው፡፡

- የሰራፕታዋ መበለት ልጅዋ ከሞት ሊነሣ አማላጅ አስነሺም አስፈልጐታል፣ ተመልሶም ሞቷል፡፡ (1ኛ ነገስት17÷19)፡፡

- የሰኑማዊቷ ልጅ ከሞት እንደተነሳ ተጽፏል፣ አማላጅ፣አስነሺ አስፈልጐታል፡፡ (2ኛ ነገስት 4÷36)፡፡ ተመልሶ ሞቷል፡፡

- የመኮንኑ ልጅ ከሞት ተነስታለች፣ አስነሺ አስፈልጓታል፡፡ (ማቴ.9÷18) ተመልሳ ሞታለች፡፡

- የቢታኒያው አላዛር ከሞት ተነስቷል፣ አስነሺ አስፈልጐታል፡፡ (ዮሐ.11÷25)ተመልሶም ሞቷል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ ቢሞቱ አስነሺ ያስፈልጋቸዋል፡፡ለኢየሱስ ክርስቶስ ግን አስነሺ፣ አማላጅ አላስፈለገውም፡፡ ሞት ይዘው ዘንድ አልቻለምና “አልቻለም” ተብሎ እንደተጻፈው፡፡ (የሐዋ.2÷24) የሞትን ጣር አጥፍቶ በስልጣኑ ያለምንም አስነሺ ተመልሶ ላይሞት ተነሣ፡፡ ክርስቶስ ከሞት ባይነሣ ኖሮ የክርስትና ሃይማኖት እና ክርስቲያኖች አይኖሩም ነበር፡፡ ለ2000 ዓመታት ቤተክርስቲያን በልበ ሙሉነት የክርስቶስን ከሞት መነሳትና ትንሣኤ እንዳለ አረጋግጣ ታስተምራለች፡፡ መቃብሩም ባዶ ነው፡፡ በታሪክ የክርስቶስ መቃብር ብቻ ነው ባዶ የሆነው፡፡

በየዓመቱ ወደቅድስተ ሀገር ኢየሩሳሌም ከየዓለማቱ ሁሉ የሚሰበሰቡ ጐለጐታ የሞትን ሽንፈትና የመቃብርን ባዶነት ለማየት ነው፡፡ የመቃብሩም ባዶነት ለመጀመሪያ ያረጋገጠችው ማርያም መቅደላዊት ናት፡፡ እርሷ ከነገረቻቸው በኋላ ጴጥሮስና ዮሐንስ የመቃብሩን ባዶነት አረጋግጠዋል፡፡ ሌሎችም ምንም እንኳን የሮማያውያን ወታደሮችን አይሁድንና ፈሪሳውያንን በገንዘብ በማታለል አልተነሳም፡፡ ደቀመዛሙርቱ ናቸው የሰረቁት ብለው የውሸት ማስተባበያ ቢሰጡም እውነት መቼም በምንም ተሸፍኖ አይቀርምና በተለያየ ጊዜ እስከ ዕርገቱ ድረስ ለ 500 ሰዎች በተለያየ ስፍራ መነሳቱን አረጋግጧል፡፡

መልዕክት

የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ስናከብር ምን ማድረግ አለብን?

- ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመምጣት፣ በማስቀደስ ያለቆረብን ንስሐ ገብተን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይገባናል፡፡

- ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና (1ኛ ቆሮ.5÷6ዓ)አሮጌው ማንነታችንን አስወግደን ወደእርሱ ልንቀርብ ይገባል፡፡

- የተራቡትን፣ የተቸገሩትን፣ የቀን ፀሐይ፣ የሌሊት ብርድ የሚፈራረቅባቸውን በመጐብኘትና ያለንን በማካፈል ማክበር ይገባል፡፡

- በእስር ቤት የታሰሩትን መጐብኘት፣

- በዓለ ፋሲካን ምክንያት አድርገን ያለመጠንና ያለልክ መኖር እራሳችንንም ለኃጢአት ከሚያጋልጥ፣ በፈተናም ከመውደቅ እራሳችንን መጠበቅ አለብን፡፡
በአጠቃላይ የክርስቶስ ትንሣኤ የእኛም ተንሣኤ ነው ብለን ማሰብ፣ እኛም የህሊና ትንሣኤ፣ ያስተሳሰብ ትንሣኤ፣ የመልካምነት ትንሣኤ፣ ከምንም በላይ የፍቅር ትንሣኤ ያስፈልገናል፡፡ እንደተናገረ ተነስቷል፡፡

ወስበሐት ለእግዚያብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ይቆየን!



እስከ ባለ 50 የሚቆይ የክርስቲያኖች ሰላምታ፣

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በዐቢይ ኃይል ወስልጣን፣
ዐሠሮ ለሰይጣን ፣
አግአዞ ለአዳም፣
ሰላም  እምእይዜሰ ኮነ ፍስሐ ወሰላም፣

ትርጉም

ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ፣
በታላቅ ኃይልና ስልጣን፣
ሰይጣንን አሰረው፣
አዳምን ነጻ አወጣው፣
ከዛሬ ጀምሮ
ደስታና ሰላም ሆነ!!!


መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንላችሁ!







No comments:

Post a Comment