Tuesday, April 17, 2012


ሰላም ለእናንተ ይሁን ዮሐ 20-26
ዳግም ትንሣኤ

ከስምንት ቀን በኃላም ደቀመዝሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፡፡ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ :: በመካከላቸው ቆሞ ሰላም ለእናተ ይሁን አላቸው……

ዳግም ትንሣኤ፡- ማለት ለአስራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ቶማስ ባለበት ለሁለተኛ ጊዜ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ ከተነሰ በኃላ በግልጥ የታየበት ዕለት ሰለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን ደግም ትንሣኤ በማለት ይህንን ዕለት ታከብረዋለች

ዳግም ትንሣኤ
-የቶማስ አለማመንና መጠራጠር ፍፁም ወደሆነና ወደ ታላቅ እምነት የተቀየረበት (ዩሐ20-27)
-በተዘጋው ቤት አምላካችን ገብቶ በእብራይስጥ ቋንቋ ‹‹ሻሎም›› ሰላም ለእናንተ ይሁን በማለት የደቀመዛሙርቱን ፍርሐት ወደ ልበ ሙሉነት የተቀየረበት ዕለት፡፡

በዚህ ባለንበ ዘመን ሁሉም ሰው ሰላም አጥቶአል
-የኑሮ ውድነት፣ የጤና ማጣት
ሁሉም ነገር ተለውጦአል ከሚሽከረከረው የሕይወት ዑደት ውስጥ ለመግባት ባለጠጋ ወይም ቆንጆሁን ፣አልያም ተማር፣ እንዲህ 
ካልሆንክ ዋጋ የለህም ወደሚል የኑሮ ስርዓት ገብተናል

የህይወት ዋጋው ገንዘብና ቆንጆነት ከሆነ ደሆችና በአካላቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ምን ይሁኑ ቅንነትና ታማኝነት ተረስተው ሰው ለቆዳው መጨነቅ ጀምሮል የዛሬውን ምስቅልቅል ኑሮ ይህ የተለወጠ ዋጋ ነው ገንዘብ እና እውቀት ሰላምን ሊያመጣ አይችልም ሰላም ግን እውነትና ገንዘብን ሊያመጣ ይችላል፡፡


ሰላማችን ማነው?

ሰላማችን ክርስቶስ ነው፡፡ ኤፌ( 2-14 )የጠብን ግድግዳ በደሙፈሰሽነት ያፈረሰ
-የተለያዩትን አንድ ያደረገ ጠላታችን ዲያብሎስን ወደጥልቁ የጣለ ወደ ቀደመ ርስታችን የመለሰን ሰለማችን ክርስቶስ ነው ፡፡
-በሁኔታዎች ሊበጠበጥና ሊታወክ የማችል እውነተኛ፣ ሰላም፣ ደስታ እና ጉስቁልና የማይለውጠው የሁል ጊዜ ሰላማችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
-ክርስቶስ ማዕበል ቢመጣም ሰላም፣ ማዕበል ባይመጣም ሰላም፣ ሊቁ አባ ጊዬርጊስ ዘጋስጫ ምገድ የማይሰባብረው መርከባችን እርሱ ብሎ እንደተናገረው ሰዎች የሰጡንን ሰላም ሰዎች ሊወስዱት ይችላሉ እዚህጋ በአንዱ ተደስተን እዚያጋ ደግሞ በሌሎች ልናዝን እንችላለን ክርስቶስን ግን ሁል ጊዜ ሰላማችን ነው ::

መልእክት
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ ከተነሳ በኃላ የደቀመዛሙርቱን ፍርሐት በማስወገድ ሰላም ሰጥቶአችኃል፡፡
-የቶማስንም የመጠራጠር ሕይወት ወደ ፍፁም እምነት እንዲለወጥ አድርጎል፡፡ በዚህ ዘመን ሰላማችን የደፈረሰብን ሰላም የሚሰጠን ማነው? በማለት የተጨነቅን ፣ገንዘብ ሰላም ሊሰጠን አይችልም ፡፡ እውቀትም የተነጠቀው ሰላማችንን ሊመልስልን አይችልም፡፡ ሰላማችን ክርስቶስ ብቻ ነው እና በተዘጋው ማንነታችን ሁሉ ፡ በመካከላችን ቆሞ ሰላም ለአንተ ይሁን፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን በማለት የተወሰደብንን ሰላም የሰላም አለቃ ፣የሰላም መገኛ ፣የሰላም አምላክ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳው ጌታ ለደቀመዛሙርቱ ሰላምን እንደሰጠ ለሁላችንም ሰላሙን ይስጠን ሰላሙን ያድለን ሰላሙን ያብዛልን አሜን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል

ዕለተ ዓርብ (ስቅለት)


ዕለተ ዓርብ (ስቅለት)

“አንዱ ስለሁሉ ሞተ” (2ቆሮ 5÷14)

ይህንን ቃል የተናገረው ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በፃፈው መልዕክቱ ነው፡፡ኢየሩሳሌም የፋሲካን በዓል ለማክበር በሽርጉድ ላይ ነች፡፡ የፋሲካ በዓል እስራኤላውያን ከ430 ዓመት የግብፅ ባህነት ነፃ የወጡበትን ቀን በማስመልከት የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡ ታዲያ ይህንን የደስታ በዓል ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ የህዝብ ምርጫ የሆነ አንድ እስረኛ መፍታት የሮማ ገዢዎች ልማድ ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም የሚገኘውና በሮማ መንግስት ሥር የሆነው እስር ቤት ብዙ እስረኞችን ይዞ ነበር፡፡ በርባን ሞት የተፈረደበትና የሞቱን ዕለት የሚጠባበቅ እስረኛ ሲሆን አደገኛ ወንበዴ በመሆኑ በብርቱ ይጠበቅ ነበር፡፡
መስፍኑ ጲላጦስ ንፁሑን ሰው አሳልፎ ለመስጠት ህሊናው ዳግመኛም የሚስቱ ማስጠንቀቂያ ይታገለው ነበር፡፡ በዚያ በአል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ዘንድ ለገዢው ልማድ ነበረው፡፡ ጲላጦስም በጣም የሚያስጨንቃቸው የነበረውን በርባንንና ኢየሱስ ክርስቶስን አነጻጽሮ ማንን ልፍታላችሁ? አላቸው፡፡ መቼም በርባንን አይመርጡም ብሎ ነው፡፡ በርባን በወንበዴነቱና በሽፍታነቱ የታወቀ ህዝቡንም ሲያስጨንቅ የኖረ፣ ቋንጃ የቆረጠ፣ ሁሉም እስራኤላዊ የተማረረበት ሰው ነው፡፡
እነርሱ ግን በቅንዓት ታውረዋልና የሚያድናቸውን ሳይሆን የሚያስጨንቃቸውን በርባንን መረጡ፣ የፈወሳቸውን ሳይሆን የቀማቸውን፣ ሰላም የሰጣቸውን ሳይሆን ያወካቸውን፣ አምላካቸውን ሳይሆን ዘራፊያቸውን መረጡ፡፡ የዓለም ምርጫ ከዚህ አያልፍምና፡፡
በርባን ከእስር ቤት ይፈታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ቦታ ይግባ/ይሰቀል/አሉ፡፡
(ማቴ 27÷17)
ወታደሮችም በርባንን ሊፈቱ ወደእስር ቤት ሲገቡ በርባን ሳይደነግጥ አልቀረም፡፡ በርባን ሆይ በነፃ ተለቀሐል አሉት፣ እርሱም እኔ በነጻ እንድወጣ ምክንያት የሆነኝ ምንድነው ቢላቸው እነርሱም እንደዋዛ ኢየሱስ በአንተ ፈንታ ሊሞት፣ አንተ ግን ነጻ ልትወጣ ተወስኗል አሉት፡፡ በርባንም በጣም ተደስቶ እስረኞችን ሲሰናበት “በሉ ሰላም ሁኑ ኢየሱስ በእኔ ምትክ ሊሞት እኔ ደግሞ በሕይወት እንድኖር ተፈርዷል” 
እያላቸው ከወህይኒ ወጣ፡፡

“አንዱ ስለሁሉ ሞተ”

ሞት ምንድነው?

አራት አይነት ሞት አለ፡-

1. ሞተ ሥጋ /የሥጋ ሞት/ ዕርደተ መቃብር ነው፡፡ ሥጋም ወደ መሬት ነፍስም ወደ እግዚአብሔር ትሄዳለች፡፡ (መክብብ 12÷7)

2. ሞተ ነፍስ /የነፍስ ሞት/ እሱን የማትሰማ ነፍስ ትሞታለች፡፡ (ዘዳ.18÷15 የሐዋ.3÷23)፣(ማቴ.25÷41)

3. ሞተ ሐጢአት /የሐጢአት ሞት/የሐጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፣
(ሮሜ 6÷23)፣(ቆላ.1÷22)፣ (ኤፌ.2÷1)

4. ሞተ ሕሊና /የሕሊና ሞት/


አምላካችን መድኃኒታችን ለምን ሞተ?


1. ቅጣታችንን ተቀብሎ ሞተ፡- የሁላችንንም በደል በራሱ ላይ አኖረ፡፡ (ኢሳ.53÷6)ስለጽድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና (ሮሜ 5÷6) ተብሎ እንተጻፈው፣ የእኛን የበደል ቅጣት እርሱ ወስዶ ተቀጣ፡፡ ማን ነው የሌላውን የቅጣት ወንጀል በዚህ ዘመን የሚወስድ? የሌላውን ቅጣት እንኳን ባንወስድ እርስ በእርሳችን መወነጃጀላችንን፣ መነካከሳችንን መቼ ተውን? እርሱ ተቀጥቶ በመስቀል ላይ እኛን ነጻ አወጣን፡፡ ቅጣታችንን ሙሉ በሙሉ ወሰደ፡፡

2. የእኛን ሞት ሞተ፡- በአንድ ሰው ምክንያት ሞት ወደዓለም ገባ ተብሎ እንደተጻፈው (ሮሜ 5÷15) የሰው ልጅ የአምላኩን የእግዚያብሔርን ትዕዛዝ ለማፍረሱ ምክንያት 5,500 ዓመት ሞት ተፈረደብን፡፡ ሞት ገዛቸው ተብሎ እንተጻፈው፡፡ ሰለ እኛ የእኛን ሞት ተገብቶ ሞተ፡፡ ሐጢአት ያላወቀውን እርሱ ስለ እኛ ሐጢአት አደረገው፡፡ (2ኛቆሮ÷15-21)ብዙ ሰዎች ሞተዋል፣ ተቀብረዋል፣ የእኛን የሐጢአት ሞት ግን መቀየር አልተቻላቸውም፡፡ በመቃብራቸውም ውስጥ የአጥንት ቅሪት አለ፡፡ ጐለጐታ ብንሔድ የጌታ መቃብር በታሪክ እስከዛሬም ድረስ ባዶ ነው፡፡ ከተለያዩ አለማትም የሚመጡ ይህንኑ ባዶ መቃብር አይተው ነው የሚመለሱት፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ለየት የሚያደርገው፡-

- የሰማያትነት ሞት አይደለም፡፡
- በድንገተኛ አደጋም አይደለም የሞተው፣ የእኛን ሞት ነው የሞተው፡፡

3. ፈውስ እናገኝ ዘንድ ሞተ፡- በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡ (ኢሳ.53÷5) እርሱ የሾህ አክሊል ተደፍቶበት እኛን የክብር አክሊል ደፋልን፡፡ ጐኑን በጦር ተወግቶና ቆስሎ ለዘለአለም ፈወሰን፡፡ ተጠማሁ እያለ እኛን የሕይወት መጠጥ አጠጣን፡፡ ማነው ለሌላው እየቆሰለ ሌላውን ሰው የሚያድን፣ የሚፈውስ፣ በዚህ ዘመን ይገኝ ይሆን? መፈወሱና መቁሰሉ ቀርቶ ማቁሰሉንና ማሳዘኑን በተውን መልካም ነበር፡፡

4. ገነትን እንወርስ ዘንድ መርገማችንን ወስዶ ሞተ፡- በእንጨት የተሰቀለ የተረገመ ነው፡፡ ተብሎ እንደተጻፈው (ዘዳ.21÷23)የመጨረሻው የእርግማን ምልክት ነው ተብሎ በሚታሰበው በመስቀል አምላካችን ተሰቀለ፡፡ የስቅላት ቅጣት የተጀመረው በፋርሳውያንና በፌንቃውያን ነው፡፡ በተለይ ግን የተጠቀሙበት ሮማውያን ናቸው፡፡ የሮም ዜጋ የሆነ ግን በምንም ምክንያት በስቅላት አይቀጣም፡፡ ይህ አይነቱ የሞት ቅጣት በጣም አስነዋሪ ወንጀሎችን በተለይም ዓመጽና ሁከት የሚያስፋፉ አይነት ወንጀል ፈጻሚዎች ብቻ በመስቀል የሚቀጡበት ነበር፡፡ አምላካችን በደል አልተገኘበትም፣ ወንጀልም አልሰራም፣ ሁከትንም አልፈጸምም አላነሳሳም፡፡ የዓመጽም ሰው አልነበረም፡፡ ጲላጦስ ሳይቀር መስክሯል፡፡ “ምንም በደል አላገኘሁበትም ነው ያለው”፡፡ በዛም ዘመን መስቀል የመጨረሻው የውርደትና የመከራ ምልክት ነበር፡፡ አሁን ግን መስቀል የድላችን ምልክት፣ ሰላማችንን ያገኘንበት፣ ጥል የተገደለበት ነውና እናከብረዋለን፡፡ (ቆላ.3÷14)፣ (ኤፌ.2÷20)፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሁላችን ሞተ

ሞቱም ቅጽበታዊ ሳይሆን ስቅለቱንና ሞቱን አስቀድሞ አረጋግጦ ተናግሯል፡፡ (ማቴ.16÷21)፣ (ማቴ.20÷17)፣ ለደቀመዛሙርቱ፡-
- የበጉ መታረድ ለመጥምቀ መለኮተ ዮሐንስ (ዮሐ.1÷29)
- ስለ በጐቹ ሕይወትን መስጠቱ (ዮሐ.10÷11-18ዓ)
- ስለ ስቅለቱ ለሕግ አዋቂው ለኒቆዲሞስ (ዮሐ.3-14)

መልዕክት

አንዱ ስለሁላችን ሞተ፣ የእኛን ቅጣት ወሰደ፣ ሞታችንን ሞተ፣ ገነትን እንድንወርስና በሕይወት እንኖር ዘንድ ሞተ፡፡ መርገማችንን ወሰደ፡፡ ወገኖቼ የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅላት ሞት ስናስብ የተጣላን ታርቀን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መሞት የሰው ልጆች የጥል ግድግዳ ፈርሶ ፍቅር የተመሰረተበት ዕለት ነውና፡፡ እኛም ጥላቻንና መነቃቀፍን በማስወገድ መኖር፣ አምላካችን ተፈጸመ ብሎ የተናገረበት ዕለት ነው፡፡ የፍቅርን እናት እናታችን ድንግል ማርያምን በደቀመዝሙሩ በዮሐንስ አማካኝነት በስጦታ የተቀበልንበት እለት ነው፡፡ (ዮሐ.19÷36)፣

- ስቅለቱንና ሞቱን ስናስብ በቀራንዮ የተደረገልንን ውለታና ቸርነት በፍፁም ልንዘነጋው አይገባም፡፡ ሁላችንም ከቤተክርስቲያን ሳንለይ በመጾምና በመጸለይ፣ የተጣላን በመታረቅ፣ ፍቅርን በመመስረትና በመስገድ ልናሳልፍ ይገባናል፡፡

- ስቅለት የ5500 ዓመት የእዳ ደብዳቤያችን የተሠረዘበትና የተወገደበት ፣መርገማችን የሐጢያታችን ቀምበር የተሰበረበት፣ የሞትና የጨለማ መጋረጃ የተቀደደበት፣ ፍፁም ፍቅር የተመሰረተበት ዕለት ነውና በየትኛውም ዓለም የምንኖር ወገኖች ከሁለም በላይ የሚበልጠው ፍቅር ነውና ፍቅርን ገንዘብ እናድርግ፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

- ለብርሃነ ትንሣኤው ያድርሰን፡፡

ለዛሬ የመረጥኩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ

“እርሱም ሐጢአት አላደረገም፣ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፣ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፣ መከራንም ሲቀበል አልዛተም፣ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፣ ለሐጢአት ሞትን፣ ለጽድቅ እንድንኖር እራሱን ራሱ በሥጋው ሐጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፣ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ፣ እንደበጐች ትቅበዘበዙ ነበርና፣ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል፡፡
(1ኛ ጴጥ.2÷22-25)ይቀጥላል፡፡


መልካም ትንሳኤ


“እንደተናገረ ተነስቷል” (ማቴ.28÷6)

እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ወረደ፣ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፣ እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፡፡ እንደተናገረው ተነስቷልና…በዚህ የለም…ኑና እዩ አላቸው፡፡ ስለ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አራቱ ወንጌላውያን በመጽሐፋቸው ስለ ትንሣኤው ምስክርነት በመስጠት አረጋግጠው ጽፈዋል፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት የመነሳቱ ማረጋገጫው ምንድነው?
- በዕለተ እሁድ ከሞት በተነሳበት ቀን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጥ ታይቷል፡፡ ለማርያም መቅደላዊት (ዮሐ.20÷11)
- ለሌሎች ሴቶች (ማቴ.28÷9) ለሁለቱ የመኤማሁስ መንገደኞች (ሉቃ.24÷13)

የኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሳቱ ለእኛ ለክርስቲያኖች ያለው ጥቅም ምንድነው?

ከሞት የመነሳታችን ማረጋገጫ ነው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሞተና እንደተነሣ ካመንን እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚያብሔር ከራሱ ጋር ያወጣቸዋልና(ያስነሳቸዋል)፡፡ (1ኛተሰ.4÷13)፣

አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነስቷል፡፡ ሞት በሰው በኩል ስለመጣ ትንሣኤውም በሰው በኩል ሆኗል፡፡ (1ኛ ቆሮ. 15÷21)ሞት ድል በመነሳት ተዋጠ ተብሎ እንደተጻፈው (1ኛ ቆሮ 15÷54)፣

- የኢየሱስ ትንሣኤ የስብከታችን ማረጋገጫ ነው፡- ትንሣኤ ሙታን ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፣ ክርስቶስ ካልተነሣ ስብከታችን ከንቱ ነው፡፡ (1ኛ ቆሮ.15÷12)፣

- ትንሣኤው የእምነታችን ማረጋገጫ ነው፡- ክርስቶስ ካልተነሣማ እምነታችን ከንቱ ነው፡፡ (ቆሮ 15÷17) ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል ሲነሣ መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በስልጣኑ ተነሣ፡፡ እንዲህ ተብሎ መቅዱሳት መጻሕፍት እንተጻፈው፣ ወተንሣአ እግዚያብሔር ከመዘንቃህ እንዋም ወከመ ኃያል ወህዳገ ወይን ወቀተለ ጸሮ በድሬሁ፣ እግዚያብሔር ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ተነሣ፡፡ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያል ሰው፣ ጠላቶቹንም በኋላው ገደለ፡፡

- (መዝ.67÷65)በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን ብዙ ሰዎች ከሞት እንደተነሱ ታሪካቸው ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ሁሉም ግን አስነሺ አላቸው፡፡

- የሰራፕታዋ መበለት ልጅዋ ከሞት ሊነሣ አማላጅ አስነሺም አስፈልጐታል፣ ተመልሶም ሞቷል፡፡ (1ኛ ነገስት17÷19)፡፡

- የሰኑማዊቷ ልጅ ከሞት እንደተነሳ ተጽፏል፣ አማላጅ፣አስነሺ አስፈልጐታል፡፡ (2ኛ ነገስት 4÷36)፡፡ ተመልሶ ሞቷል፡፡

- የመኮንኑ ልጅ ከሞት ተነስታለች፣ አስነሺ አስፈልጓታል፡፡ (ማቴ.9÷18) ተመልሳ ሞታለች፡፡

- የቢታኒያው አላዛር ከሞት ተነስቷል፣ አስነሺ አስፈልጐታል፡፡ (ዮሐ.11÷25)ተመልሶም ሞቷል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ ቢሞቱ አስነሺ ያስፈልጋቸዋል፡፡ለኢየሱስ ክርስቶስ ግን አስነሺ፣ አማላጅ አላስፈለገውም፡፡ ሞት ይዘው ዘንድ አልቻለምና “አልቻለም” ተብሎ እንደተጻፈው፡፡ (የሐዋ.2÷24) የሞትን ጣር አጥፍቶ በስልጣኑ ያለምንም አስነሺ ተመልሶ ላይሞት ተነሣ፡፡ ክርስቶስ ከሞት ባይነሣ ኖሮ የክርስትና ሃይማኖት እና ክርስቲያኖች አይኖሩም ነበር፡፡ ለ2000 ዓመታት ቤተክርስቲያን በልበ ሙሉነት የክርስቶስን ከሞት መነሳትና ትንሣኤ እንዳለ አረጋግጣ ታስተምራለች፡፡ መቃብሩም ባዶ ነው፡፡ በታሪክ የክርስቶስ መቃብር ብቻ ነው ባዶ የሆነው፡፡

በየዓመቱ ወደቅድስተ ሀገር ኢየሩሳሌም ከየዓለማቱ ሁሉ የሚሰበሰቡ ጐለጐታ የሞትን ሽንፈትና የመቃብርን ባዶነት ለማየት ነው፡፡ የመቃብሩም ባዶነት ለመጀመሪያ ያረጋገጠችው ማርያም መቅደላዊት ናት፡፡ እርሷ ከነገረቻቸው በኋላ ጴጥሮስና ዮሐንስ የመቃብሩን ባዶነት አረጋግጠዋል፡፡ ሌሎችም ምንም እንኳን የሮማያውያን ወታደሮችን አይሁድንና ፈሪሳውያንን በገንዘብ በማታለል አልተነሳም፡፡ ደቀመዛሙርቱ ናቸው የሰረቁት ብለው የውሸት ማስተባበያ ቢሰጡም እውነት መቼም በምንም ተሸፍኖ አይቀርምና በተለያየ ጊዜ እስከ ዕርገቱ ድረስ ለ 500 ሰዎች በተለያየ ስፍራ መነሳቱን አረጋግጧል፡፡

መልዕክት

የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ስናከብር ምን ማድረግ አለብን?

- ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመምጣት፣ በማስቀደስ ያለቆረብን ንስሐ ገብተን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይገባናል፡፡

- ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና (1ኛ ቆሮ.5÷6ዓ)አሮጌው ማንነታችንን አስወግደን ወደእርሱ ልንቀርብ ይገባል፡፡

- የተራቡትን፣ የተቸገሩትን፣ የቀን ፀሐይ፣ የሌሊት ብርድ የሚፈራረቅባቸውን በመጐብኘትና ያለንን በማካፈል ማክበር ይገባል፡፡

- በእስር ቤት የታሰሩትን መጐብኘት፣

- በዓለ ፋሲካን ምክንያት አድርገን ያለመጠንና ያለልክ መኖር እራሳችንንም ለኃጢአት ከሚያጋልጥ፣ በፈተናም ከመውደቅ እራሳችንን መጠበቅ አለብን፡፡
በአጠቃላይ የክርስቶስ ትንሣኤ የእኛም ተንሣኤ ነው ብለን ማሰብ፣ እኛም የህሊና ትንሣኤ፣ ያስተሳሰብ ትንሣኤ፣ የመልካምነት ትንሣኤ፣ ከምንም በላይ የፍቅር ትንሣኤ ያስፈልገናል፡፡ እንደተናገረ ተነስቷል፡፡

ወስበሐት ለእግዚያብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ይቆየን!



እስከ ባለ 50 የሚቆይ የክርስቲያኖች ሰላምታ፣

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በዐቢይ ኃይል ወስልጣን፣
ዐሠሮ ለሰይጣን ፣
አግአዞ ለአዳም፣
ሰላም  እምእይዜሰ ኮነ ፍስሐ ወሰላም፣

ትርጉም

ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ፣
በታላቅ ኃይልና ስልጣን፣
ሰይጣንን አሰረው፣
አዳምን ነጻ አወጣው፣
ከዛሬ ጀምሮ
ደስታና ሰላም ሆነ!!!


መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንላችሁ!







“እያዩት ወደሰማይ ዐረገ”(ሉቃ 24÷50 የሐዋ 1÷9)


በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አ፩ዱ አምላክ አሜን

“እያዩት ወደሰማይ ዐረገ”(ሉቃ 24÷50 የሐዋ 1÷9)
ዕርገት

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነሥቶ
የትንሣኤያችን በኩር የሆነው ጌታ በመቃብሩ ቦታ
- ለማርያም መቅደላዊት እና ለሌሎችም ሴቶች (ማቴ 28÷1 የሐዋ 2÷1)፡፡
- ለኤማውስ መንገደኞች( ሉቃ 24÷13)
- ለደቀማዛሙርቱ በተዘጋ ቤት (ዮሐ 20÷8)
- በጥብርያዶስ ባህር ለደቀመዛሙርቱ ዮሐ 21÷4 
ሥርዓትን እያስተማረ አልፎ አልፎም በግልጥ እየታየ ፍርሐታቸውን እያስወገደ አይሁድ እንደሚሉት ሥጋውንም ደቀመዛሙርቱ እንዳልሰረቁት ይልቁንም በሞት ላይ ሥልጣንኑን አሳይቶ መቃብሩን ባዶ አድርጐ በትንሣኤው አለት ላይ ያቆመን፣ ሞት በእርሱ እንደተሸነፈ የማይታየው እየታየ፣ ዘመን የማይቆጠርለት፣ ዘላለማዊ ጌታ የማይዳሰሰው እየተዳሰሰ ለ40 ቀናት ያክል ቆይቶ ተከታዮቹን ሐዋርያትን ወደቢታንያ አወጣቸው፡፡ እያዩት በምስጋና ወደሰማይ ዐረገ፡፡ እንዲህ ተብሎ በነብዩ ዳዊት እንደተፃፈው፡- “ዐረገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለቀርን ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ” እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዐረገ፣ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ፣ ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ (መዝ 46÷5)

አምላካችን ወደሰማይ ከማረጉ በፊት ደቀመዛሙርቱን ምን አዘዛቸው?

1. ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡ (ሉቃ 24÷48) ደቀመዛሙርቱ ያዩትንና የሰሙትን ሞትን አሸንፎ የተነሣውን ጌታ ለዓለም ሁሉ ምስክሮች ሆነዋል፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የዓላውያንን ነገሥታት፣ የቄሳሮችን ዛቻና ማስፈራሪያ አንዳችም ሳይፈሩ ከምድር ዳርቻ እስከምድር ዳርቻ ድረስ ሁሉን እያጡና መከራ እየተቀበሉ፣ እየታሰሩና እየተገረፉ ምስክሮች ሆነዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ በኋላ ስሙን አትጥሩና በስሙም አታስተምሩ እያሏቸው በሸንጐ ፊት ሲያቆሟቸው፣ ሲገርፏቸው ደስ እያላቸው ከሸንጐ ፊት ይወጡ ነበር፡፡ (የሐዋ 5÷40)፡፡ ስለ ስሙ ምስክር መሆን መነቀፍና መታሰር፣ መደብደብ እንዴት ደስ ይላል!፡፡ እኛም እንደ ደቀመዛሙርቱ ማንንም ሳንፈራ አፋችንን ሞልተን ስለ ስሙ እየመሰከርን ሁሉን ብናጣም ሞታችንን በሞቱ ድል የነሣልንን የሚቃወመንን ጠላታችንን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ያስወገደልንን፣ እረፍትና ሰላም የሰጠንን፣ ጨለማውን ገፎ ብርሐንን ያጐናፀፈንን፣ ያለፈውን ታሪካችንን በነበር ላስቀረልን ምስክሮች እንሁን፡፡

2. አጽናኙን እልክላችኋለሁ (ዮሐ 15÷26)፡-
- በአህዛብና በዓላውያን ነገሥታት ፊት ሲቆሙ እውነትን እንዲናገሩ የሚያፅናና ኃይል፣
- ከተዘጋ ቤት ወደ ሠገነት እንዲቆሙ የሚያደርግ ኃይል፣
- ልበ ሙሉ ሆነው ከጥርጥር ወደ ፍፁም እምነት፣ ከፍርሃት ወደ ድፍረት እንዲሸጋገሩ የሚያበረታታ አጽናኝ ኃይል እልክላችኋለሁ፡፡
ይህ ኃይል በዘመናችን በጣም ስለሚያስፈልገን በፍፁም መዘንጋት የለብንም፡፡ እውነትን ለመናገርና ለመመስከር፣ ፍርሐታችን እንዲወገድልን ከፈለግን ይህንን ኃይል ዓለም ሳይሆን የሚሰጠን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን አውቀን ጌታ ሆይ እኔን ልጅህ ያንተን ኃይል አጥቼ ደክሜያለሁ፣ ከእኔ የሆነ ኃይል ምንም የለምና ከእኔ አትራቅ፡፡
- ባስልኤልንና ኤልያብን በጥበብ መንፈስ የሞላህ (ዘፀ36÷2)
- ሶምሶንን በጾርዓና በኤሽታኦል ያነቃቃህ (መሳ 14÷18)
- ለደቀመዛሙርቱ ኃይልህን ልከህ 71 ቋንቋ የገለጥክ፣ በየዘመናቱ የተመረጡ አገልጋዮችህ ያፅናናህ፣ የእውነትን ቃል እየላክ ያበረታታህ እኛም እንድንበረታ ኃይልህን ከአርያም ላክልን፣

3. በኢየሩሳሌም ቆዩ (ሉቃ 24÷49)፡- ደቀመዛሙርቱ ከቢታንያ ወደ
ኢየሩሳሌም ተመልሰው በአንድ ልብ ሆነው በኢየሩሳሌም ቀዩ፡፡ በመቆየታቸውም
ሰማያዊ ኃይል አገኙ፡፡
እኛ ሰማያዊ ኃይል ለማግኘት የት እንቆይ?
- በኢየሩሳሌም ቤተክስቲያን መቆየት ያስፈልገናል፣
- በአንድ ልብ ሆነን በቤታችን፣ በአገልግሎታችን፣ በዘር፣ በጐሣ ሳንከፋፈል ይኸ እንዲህ ነው፣ ያ ደግሞ እንዲህ ነው ሳንል ከኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን የወጣንም እንመለስ፣
- ሰዎች ባይመቹንም፣ ክፉዎች ልባችንንን ቢያቆስሉንም፣ ሰዎች እንጂ ያልተመቹን ክርስቶስና ቤተክርስቲያን ሁልጊዜ ይመቹናል፡፡ ስለዚህም ከኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን አንውጣ፡፡ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እየበላንና እየጠጣን፣ እያገለገልን፣ ያደግንባት የእኛ ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያናችን ብናዝን የምንጽናናባት፣ አእምሮአችን የሚያርፍባት፣ ሰላም የምናገኝባት ኢየሩሳሌም ቤትክርስቷያናችን ናት፡፡

ማጠቃለያ

አምላካችን የማዳን ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ለተከታዮቹ ደቀመዛሙርት ምስክሮቼ ናችሁ፡፡ አጽናኙን እልክላችኋለሁ፡፡ “አንትሙ ንበሩ በሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ሃይለ እማርያም፡፡ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሎ አዘዛቸው፡፡

በመጨረሻም ወደሰማይ ሲያርግ እጆችንም አንስቶ ባረካቸው፡፡ (ሉቃ 24÷51)
በብሉይ ኪዳን ተፅፎ እንደምናገኘው፡- አባታችን አብርሃምን ባርኮ ያበዛ(ዘፍ12÷1)፣ ያዕቆብን በያቦቅ ወንዝ ሲባረክ ያደረ (ዘፍ35÷9)፣ ያቤጽን ባርኮ ሀገሩን ያሰፋ(1ኛ ዜና 4÷9)፣ አምስቱን እንጀራ፣ ሁለቱን ዓሣ አብዝቶ የባረከ ጌታ ዛሬም በኑሯችን አብዝቶ የሚባርከን፣ ሥራችንን እንድንሠራ በበረከት ያጣነውን ደስታ የሚመልስልን፣ ባርኮ በበረከት ወደሚያትረፈርፍልን፣ ጉድለትን ሳይሆን ሙላትን፣ ማጣት ሳይሆን በረከትን ወደሚሰጠን ደቀመዛሙርቱ ዓይኖቻቸውንም ወደላይ ትኩር ብለው እንደተመለከቱት እንደሐዋርያት ማየት ይጠበቅብናል፡፡ እውነት ነው እርሱን ማየት ከሁሉም ይበልጣልና ወደሰማይ ያረገውን ጌታ አይናችንን አንስተን እንይ፡፡

በዚህ ዘመን አይኖቻችን ምን ይሆን የሚመለከቱት?

ገንዘብ፣ ጌጣጌጥ ወገኖቻችንን በክፋት የራሳችንን ኃጢአት ሳንመለከት የሌሎችን በማየት ብቻ የምንኖር ሥጋዊ ነገሮችን ብቻ የምናይ ከሆነ የክርስቶስ ምስክሮች መሆን አንችልም፡፡ አጽናኙም መንፈስ ወደእኛ በፍፁም ሊመጣ አይችልም፡፡ በኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን መቆየት እጅግ አሰቸጋሪ ነው የሚሆንብን እንደ ደቀመዛሙርቱ ሳንበታተን በአንድ ልብና መንፈስ ሆነን የእግዚአብሔርን ኃይልና በረከት እንጠብቅ፡፡ የሰውን ልጅ ለማዳን ወደዚህ ምድር የመጣው፣ካለ ምንም አስነሺ የተነሣው፣ የማዳን ሥራውን ከፈፀመ በኋላ ደቀመዛሙርቱ እያዩት በሥልጣኑ በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

እኛም አይናችንን ከልባችን ጋር አንሥተን ምድራዊውን ነገር ማየት ትተን ወደሰማይ 
ያረገውን ጌታ እርሱን እንድናይ ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር

"ዘመኑን እየዋጃችሁ በጥበብ ተመላለሱ" ቆላ4፡5